የስልጤ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት የለሊትና የምሽት የንግድ አገልግሎት መስጠትን አስገዳጅ የሚያደርግ ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት አደረገ!

የስልጤ ዞን አስተዳደር ምክር ቤት በዞኑ በሚገኙ ከተሞች የምሽትና የሌሊት የንግድና የአገልግሎት ሥራዎች ቀጣይነት፣ ወጥነትና ተደራሽነት እንዲኖራቸው የሚያስችል ረቅቅ ደንብ አውጥቷል።

ደንቡ የከተሞቹን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማሳደግ፣ የሥራ ባህልን ለማዳበር፣ የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊና ተሳለጠ ለማድረግ እና ለህብረተሰቡ የተሻለ የአገልግሎት አማራጭ ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የደንቡ ረቂቅ በስልጤ ዞን ፍትሕ መምሪያ ኃላፊ አቶ ሬድዋን ኑሪ ለዞኑ ካቢኔ አባላት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይቱም በዞኑ የንግድና የአገልግሎት ዘርፎች የሚታዩ የሥራ ሰዓት አለመጠበቅ፣ከሚገባው በፊት መዝጋት፣ በበዓላት ወቅት ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ማቋረጥ እና 24 ሰዓት አገልግሎት ሊሰጡ የሚገባቸው ተቋማት ዝግ መሆን ያሉ ችግሮች ተነስተዋል።

የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል እንደገለጹት ረቅቅ ደንቡ የዞኑን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማጠናከር፣ የሥራ ባህልን ለማዳበር እና የከተሞችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የተዘጋጀ መሆኑ ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር የንግድ ተቋማት የሸማቹን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ ተሟላ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እና የከተሞችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ረቂቅ ደንቡ የተዘጋጀ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የስልጤ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ እስማኤል ዲላ በበኩላቸው፣ ደንቡ በዞኑ የሚገኙ ከተሞችን የመሰረተ ልማት ዕድገት የሚመጥን ዘመናዊና የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት ለመፍጠር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አቶ እስማኤል አክለውም በየደረጃው ካሉ የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ተወያይቶ ወደ ተግባር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አቶ ሬድዋን ኑሪ በረቂቅ ደንቡ ላይ ከካቢኔ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎችና ማብራሪያ በሚፈልጉ ጉዳዮች ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

ቀጣይ ውይይቶች በማድረግ የሚገኙ ግብዓቶችን በማካተት ደንቡ በሕጋዊ ሂደት ጸድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባም ገልጸዋል።

በመጨረሻም የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙበራ ከማል የቀረቡ ሀሳቦችን በማጠቃለል ረቂቅ ደንቡ ለቀጣይ የማጽደቅ ሂደት እንዲተላለፍ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡(ስዞመኮ)

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *