በወራቤ ከተማ ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ የተገነባው የምርት ማሳያና መሸጫ ማዕከል ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ርክክብ ተደረገ!

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ አማካኝነት በወራቤ ከተማ የተገነባው የG+1 የምርት ማሳያና መሸጫ ማዕከል ግንባታ ተጠናቆ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ርክክብ ተደርጓል።

በዚህም በወራቤ ከተማ የሚገኙ ስምንት አምራች ኢንተርፕራይዞች የሼዶቹን ቁልፍ ተረክበዋል።

በርክክብ በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ኢሳ እንደገለጹት፡ መንግሥት ለአምራች ዘርፉ ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ለመካከለኛው ገበያና ለወደብ ካለው ቅርበት አንጻር ለኢንዱስትሪ ልማት ከፍተኛ የንጽጽር ብልጫ እንዳለው የጠቆሙት የቢሮ ኃላፊው የተገነቡት ሼዶች የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሬ ለማስገኘት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዙ ተናግረዋል።

የክልሉ ህዝብ ያለው የስራ ፈጠራ ክህሎትና አዳዲስ የቴክኖሎጂ ሃሳቦችን ወደ ተግባር የመቀየር አቅም ለዘርፉ እድገት መሰረት እንደሆነ ጠቁመዋል።

የሼድ ግንባታው ከዚህ ቀደም የነበረውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት የታለመ እንደሆነና በወራቤ ከተማና በሌሎች አራት የክልሉ ከተሞች ተመሳሳይ ግንባታዎች ተገንብተው ለኢንተርፕራይዞች እየተላለፉ መሆኑን አመላክተዋል።

በዛሬው ዕለትም በወራቤ ከተማ ስምንት አምራች ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ለገበያ ማቅረብ የሚያስችላቸውን ሼዶች መረከባቸውን ተናግረዋል።

አቶ ሙስጠፋ አክለውም ሼዶቹን የተረከቡት ኢንተርፕራይዞች በቀጣይ አቅማቸውን በማሳደግ ወደ ከፍተኛ የኢንቨስትመንት ደረጃ በመሸጋገር ቦታውን ለሌሎች አዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ማስተላለፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የስልጤ ዞን ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ መምሪያ ዋና ኃላፊ አቶ አብዱረህማን ወርቅቾ እንደገለጹት የሥራ አጥነትን ችግር ለመቅረፍና ኢንተርፕራይዞችን ለማጠናከር መንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው።

ፕሮጀክቱ መጠናቀቁ በብልጽግና ፓርቲ የተያዘውን “የጀመርነውን እንጨርሳለን” የሚል መርህ ያሳየ መሆኑን ገልጸው በከተማዋ ለሚገኙ ወጣቶችና ኢንተርፕራይዞች ትልቅ የሥራ ተነሳሽነት የሚፈጥር መሆኑንና በቀጣይም ለዘርፉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ኃላፊው አያይዘውም ኢንተርፕራይዞች የተዘጋጀላቸውን ምቹ የሥራ ቦታ በመጠቀም፣ ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደግ፣ ቴክኖሎጂን በመጠቀምና የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኙ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ግንባታው ጥራት ባለው መልኩ እንዲጠናቀቅና የመንግሥት ሀብት እንዳይባክን የክልል የቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ላደረጉት ክትትልና ድጋፍ በዞኑ ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ይህ የምርትና መሸጫ ሼድ ኢንተርፕራይዞች ካሉባቸው የቦታ ጥበትና የምርት ማከማቻ ችግሮች በመላቀቅ በነፃነትና በስፋት እንዲሰሩ ያስችላቸዋል ብለዋል።

የወራቤ ከተማ አስተዳደር ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራዝ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዱራዛቅ ሸ/ኑሪ በበኩላቸው ህንጻው በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት ለረጅም ጊዜ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ቆይቶ እንደነበረ አስታውሰው በ2017 ዓ.ም በክልሉ የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ግንባታው በዘንድሮው ዓመት ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን አብራርተዋል።

ሕንፃው ከ2.8 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት እንደሆነና ይህም መንግሥት ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለኢንተርፕራይዞች እድገት የሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ሲሉ አቶ አብዱረዛቅ ተናግረዋል።

የሕንጻው ግንባታ መጠናቀቅ ለበርካታ ኢንተርፕራይዞች የመሥሪያና የመሸጫ ቦታዎችን በማመቻቸት እረገድ የጎላ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

የክልል ስራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ምክትል ሀላፊ እና የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ ዙልፋ አለዊን ጨምሮ ሌሎችም የዞንና የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በዕለቱም የቢሮው ምክትል ኃላፊ በሆኑት ወ/ሮ ዙልፋ አለዊ አማካኝነት በበጎ ፈቀድ አገልግሎት ለአንድ የአካል ጉዳተኛ ሙሉ ፓኬጅ ያለው ግምቱ እስከ 26,000 ብር የሚያወጣ ዘመናዊ የሊስትሮ መስሪያ ማቴሪያል አበርክተዋል።

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *