ሀገራዊ የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር በወራቤ ከተማ ተካሄደ!

“ተስፋን እንትከል” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደውና በአንድ ጀምበር 800 ሚሊየን ችግኝ የመትከል ግብ ያለው የ2018 ዓ.ም የአንድ ጀምበር ሀገራዊ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር እንደ ወራቤ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች በጋራ በመሆን ችግኝ ተክለዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ እንስፔክሽንና ስነ-ምግባር ኮሚሽን ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አብዱልዋሪስ ጀማል እንደ ሀገር ስምንት መቶ ሚሊየን በክልላችን ደግሞ አስር ሚሊየን ችግኝ የሚተከል መሆኑን በመግለፅ በዚህም 1.2 ሚሊየን የህበረተሰብ ክፍሎች የሚሳተፉበት ሲሆን እንደ ክልል 3ሺህ 36 ሄክታር የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፉት ዓመታት እንደ ሀገር በርካታ ችግኞች መተከላቸውን ያነሱት ሃላፊዉ በዚህ አበረታች ዉጤት ማስገኘቱን ሃላፊዉ ጠቁመዋል።

ችግኝን መትከል ምግብን መትከል፣ የሰዎች ጤንነት ዋስትና እንዲያገኝ ማድረግ፣ አካባቢን መጠበቅ፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሆነና ሌሎችም ፋይዳዎች እንዳሉት አቶ አብዱልዋሪስ አንስተዋል።

በሌላ በኩል የወራቤ ከተማ አስተዳደር ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ናስር ቡሽራ በበኩላቸው ችግኝ መትከል የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ምርትና ምርታማነትን የሚጨምር ነዉ።

አቶ ናስር አክለውም ተስፋን እንትከል በሚል ሃሳብ የሚደረገዉ የዘንድሮዉ የችግኝ ተከላ መርሃግብር ረዥም ዕይታን የሚጠይቅ መሆኑን በመጥቀስ ችግኝንና መልካም ዘርን በመትከል ለቀጣይ ትዉልድ ተስፋን የማሰብ ስራ መስራት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ሙህዲን ሁሴን፣ የስልጤ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ሃላፊ አቶ አብዱልሰመድ አብደላ፣ የወራቤ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የማዛጋጃ ቤቱ ሃላፊ አቶ ሻፊ ሙዜ፣የወራቤ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ነስሬ አማን፣ የብልጽግና ፓርቲ አደረጃጀት ዘርፍ ሃላፊ አቶ ባህረዲን ሀሰን፣ የክልል፣ የዞንና የከተማው አመራሮችና የመንግሥት ሰራተኞች፣ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች እና ሌሎችም ተሳትፈዋል።

Comments

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *